ይህ የተገጸው በፌዴራልና በክልል ደረጃ ከሚገኙ የዳያስፖራ ባለድርሻ አካላት ጋር የ2014 በጀት ዓመት ስራ አፈጻጸም በተገመገመበት፣ ከዳያስፖራ ተሳትፎ አንጻር ያጋጠሙ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው በተዳሰሱበትና ቀጣይ አቅጣጫዎች በተመላከቱበት የምክክር መድረክ ላይ ነው ።
በመድረኩ መክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሐመድ እንድሪስ ባስተላለፉት መልዕክት በውይይት መድረኩ ላይ ለመሳተፍ የአገልግሎቱን ጥሪ አክብረው ለተገኙ የክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነሮችና የዳያስፖራ ማስተባበሪያ ቢሮ ሀላፊዎች፣ የፌዴራልና የክልል ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም የዳያስፖራ ማህበራት አመራሮች ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ኢትዮጵያ በዳያስፖራ ጉዳይ ላይ መስራት ከጀመረች ሁለት አስርታት በመቆጠር ላይ መሆናቸውንም ጠቅሰው፣ በእነዚህ ዓመታት በዳያስፖራ ተሳትፎ ሊገኙ የሚችሉ ወረቶችን በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ መጠቀም የሚያስችሉ አደረጃጀቶች፣ የአሰራር ስርዓቶችና የህግ ማዕቀፎች በመጀታቸውን ገልጸዋል። በተፈጠረው ምቹ ሁኔታም የዳያስፖራው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ በማደግ ላይ የሚገኝ መሆኑን አንስተው፣ በተያዘው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ብቻ ዳያስፖራው ለልዩ ልዩ ሀገራዊ ጥሪዎችና ፕሮጀክቶች ያደረገው የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ ከ1.37 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። አክለውም ዳያስፖራው ከሀገሩ ጋር ያለው ግንኙነት በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት በመጀመሩ ወቅታዊ ሁኔታዎችን የሚሻገርና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስቀድም የዳያስፖራ ማህበረሰብ እየተፈጠረ መምጣቱን ገልጸዋል። የዳያስፖራውን ዕምቅ አቅም በማስተባበር ተሳትፎውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና ኢትዮጵያ ከዳያስፖራዋ የምትፈልጋቸውን ወረቶች አሟጦ ለመጠቀም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ሀላፊው ጥሪ አቅርበዋል።
ለሁለት ቀናት በቆየው መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት፣ የክልልና ከተማ አስተዳደሮች ዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች የ2014 በጀት ዓመት የአፈጻጸም ሪፖርቶች፣ በየክልሎቹና ከተማ አስተዳደሮቹ የሚገኙና ዳያስፖራውን ሊያሳትፉ የሚችሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሁም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የ2015 በጀት ዓመት ረቂቅ ዕቅድ በየተቋማቱ የበላይ አመራሮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከጤና እና ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የመጡ ተወካዮች በየዘርፋቸው ለዳያስፖራ ተሳትፎ ምቹ የሆኑ አማራጮችን አቅርበዋል።
በየተቋማቱ በቀረቡ ሰነዶች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎ ማዳበሪያ ሀሳቦች የቀረቡ ሲሆን፣ ለተነሱ ጥያቄና አስተያየቶችም በሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ በተላለፈው መልዕክት የክልልና የከተማ አስተዳደር ዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶችን ማጠናከር፣ የተደራጀ መረጃ መያዝ፣ የዳያስፖራ ማህበራትን መደገፍ፣ በዳያስፖራ ተሳትፎ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መለየትና ወቅታዊ መፍትሔ መስጠት በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸው የተመላከተ ሲሆን፣ በቅርቡ የሚጀመረው ሁለተኛው ዙር ከኢድ እስከ ኢድ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት ጥሪ ውጤታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል።
ባለድርሻ አካላቱም በበኩላቸው የዳያስፖራ ተሳትፎን ለማሳደግ የጀመሯቸውን ቅንጅታዊ አሰራሮች አጠናክረው እንደሚቀጥሉና በየአካባቢያቸው ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለዳያስፖራው ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

