በኦሮሚያ ክልል ዳያስፖራው በክልሉ ልማት በስፋት መሳተፍ እንዲችል ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2016(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ዳያስፖራው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የልማት ስራዎች ላይ በስፋት እንዲሳተፍ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ገለጹ።
የኦሮሚያ ክልል የዳያስፖራ የኢንቨስትመንት ተሳትፎና የማህበረሰብ ልማት የጋራ ምክክር መድረክ በክልሉ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ተካሂዷል።
የክልሉ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር አብዱልዓዚዝ ዳውድ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የክልሉ ዳያስፖራ በኢንቨስትመንትና በልማት መሳተፍ እንዲችል ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
የክልሉ ዳያስፖራ በበርካታ ዘርፎች ላይ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
አሁንም ዳያስፖራው የሚያደርገው ተሳትፎ በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር የራሱን አሻራ ማሳረፍ አለበት ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ የክልሉ መንግስት የዳያስፖራውን የልማትና የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል ዳያስፖራ ተሳትፎ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ አሚን ጁንዲ፣ የክልሉ ዳያስፖራ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎች ላይ በስፋት እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል።
በእስካሁኑ ሂደትም ከክልሉ አልፎ በሀገር ደረጃ ትልልቅ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ እየተሳተፉ ያሉ ዳያስፖራዎች በርካታ ናቸው ብለዋል።
በቀጣይም የክልሉ ዳያስፖራ በሀገር ልማትና እድገት ላይ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችል አስፈላጊ ድጋፎች እንደሚደረጉም ጠቅሰዋል።
የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዲስትሪ ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ ደነቀው በበኩላቸው ቢሮው ለዳያስፖራው ምቹ የሆኑ አሰራሮች እየዘረጋ መሆኑን ገልጸዋል።
የዳያስፖራ አባላትም ከአገልግሎት ዘርፍ ይልቅ በማምረቻው ዘርፍ በመሰማራት ለዜጎች ስራ መፍጠር የሚያስችሉ የልማት ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ መክረዋል። ቢሮው በሚችለው አቅም ሁሉ የልማት ተሳትፎ ማነቆ ሆነው የቆዩ ችግሮችን በመፍታት ረገድ የጀመረውን ስራ ያጠናክራል ብለዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ዳያስፖራው በሚችለው አቅም ሀገሩን እንዲያግዝ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር አቶ በላይ አቅናው ናቸው። አገልግሎቱ ከተለያዩ ሀገራት ምርጥ ተሞክሮዎችን ቀምሮ የዳያስፖራውን መብትና ጥቅም ለማስከበር በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል። በውይይት መድረኩ ላይ በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ የዳያስፖራ አባላት ተሳትፈዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *