የኦሮሚያ ዳያስፖራ ማህበር በአዳማ እያስገነባ ያለውና 85% የተጠናቀቀው የሶሌ ቡኡረ ቦሩ ትምህርት ቤት ጉብኝት ተካሄደ።
በጉብኝቱ ላይ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታው ክቡር ዶ/ር ብርሀኑ ሌንጂሶ፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሐመድ እንድሪስ፣ የአዳማ ከተማ ምክትል ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ ሂንሴኔ መሐመድ፣ በኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት የዳያስፖራ ማስተባበሪያ ሃላፊ ክቡር አቶ አሚን ጁንዲ እንዲሁም የኦሮሚያ ዳያስፖራ ማህበር አመራሮችና አባለት ተገኝተዋል። በወቅቱም ክቡር ዋና ዳይሬክተሩ ባስተላለፉት መልዕክት በሀገር ልማት ውስጥ ትርጉም ያለው ተጽዕኖ ለማምጣት ዳያስፖራው ትምህርት ቤቶችን በመሳሰሉ ትውልድን በሚገነቡ ስራዎች ላይ መሳተፉ የሚበረታታ ተግባር መሆኑን አንስተው፣ በዚህ ረገድ የኦሮሚያ ዳያስፖራ ማህበር እያከናወናቸው ያሉ ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል። በግልም ሆነ በቡድን የሚከናወኑ ትውልድን የመገንቢያ ተቋማት ስራዎች በሌሎችም አካባቢዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበው፣ ለስራው መሳካት አገልግሎቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። በጉብኝቱ ላይ ለተሳተፉ የኦሮሚያ ዳያስፖራ ማህበር አባላት ክልሉንና ሀገራቸውን በሚኖሩበት አካባቢ እንዲያስተዋውቁ ጥሪ መቅረቡን ከኦሮሚያ ዳያስፖራ ማህበር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

