አዲስ አበባ ሰኔ 7/2015(ኢዜአ):- ባለሀብቶች በኦሮሚያ ክልል ያለውን እምቅ ሀብት በመጠቀም በኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲሰማሩ ምቹና ቀልጣፋ አሰራር መዘርጋቱን የክልሉ ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው በመገባደድ ላይ ባለው በጀት ዓመት 5 ሺህ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ተቀብሎ ከ3 ሺህ 600 በላይ ለሚሆኑት ፈቃድ መስጠቱን ገልጿል።
የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ አሕመድ እዲሪስ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሰሜኑ ጦርነት በስምምነት ከተፈታ በኋላ የክልሉ ኢንቨስትመንት መነቃቃት ማሳየቱን አስታውቀዋል፡፡
በርካታ ባለሃብቶች በክልሉ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎታቸው መጨመሩንም ነው የቢሮ ሀላፊው የተናገሩት።
በተያዘው በጀት ዓመት በክልሉ ከ3 ሺህ 600 በላይ ለሚሆኑ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸው፤ በክልሉ ኢንቨስትመንት ቦርድ ፈቃድ ያገኙ ባለሀብቶች በግብርና፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በማኑፋክቸሪንግና በአገልግሎት ዘርፍ የሚሰማሩ ናቸው ብለዋል፡፡
ባለሀብቶቹ በአጠቃላይ ከ186 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገባቸውን ጠቁመው፤ ፕሮጀክቶቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ ሲገቡ ከ679 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል የመፍጠር አቅም እንዳላቸው ነው አቶ አህመድ የጠቆሙት።
በኦሮሚያ ክልል በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያለውን ቢሮክራሲ ለማሳጠር በክልሉ ፕሬዝዳንት በኩል ኃላፊነት መወሰዱን ጠቁመው፤ ይህም ስራ በሸገር ከተማ ላይ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
አንድ ባለሀብት ወደ ሸገር ከተማ ለኢንቨስትመንት ሲመጣ በፍጥነት መሬት በመረከብ ወደ ትግበራ መግባት የሚችልበት አሠራር ተግባራዊ መደረጉን አመልክተዋል።
በመጪው ዓመትም በርካታ ባለሀብቶችን ለመሳብ አሠራሮችን ቀልጣፋ የማድረግ እና የማዘመን ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አቶ አህመድ እዲሪስ ገልጸዋል።
በዘንድሮ ዓመት ፈቃድ ከተሰጣቸው ባለሀብቶች መካከል 92 የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ጥያቄ ያቀረቡ፣ 1 ሺህ 502 ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች፣ 47 ዩኒየኖች እንዲሁም 1 ሺህ 680 የአገር ውስጥ እና የዳያስፖራ ባለሀብቶች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።

